
በወጣት የሴት አርበኞቻችን ላይ የአብይ አህመድ ሰራዊት የፈጸመውን አረመኔያዊ የጭካኔ ወንጀል አጥብቀን እንኮንናለን፣ እናወግዛለን
የአማራው ሕዝብ በኢትዮጵያ በየትኛውም ሥፈራ በሰላም እንዳይኖር በወያኔና በብልጽግና አገዛዝ ተወስኖ፣ እጅግ ሰቃይና መከራ የተሞላበት ህይወት ሲገፋ ቢቆይም አሁን ደግሞ ከምድረ ገጽ በተለያዩ ስልታዊ መንገዶች ለማጥፋት፣ ባህሉን፣ ቁንቋውን በመለወጥ የስቃይ ዘመኑ ሲበዛበት፣ ህልውናውን ለማስከበር የሞት ሽረት የህልውና ትግል ከጀመረ ሁለት አመታት በላይ አልፎታል። ይህም አልበቃ ብሎ ጥዋት ማታ ሰላማዊ ሰዎችን በድሮን ቦምብ እና በከባድ መሳሪያ ይደበደባል በዚህም አቅመ ደካሞችና ህጻናት እንደ ቅጠል እየረገፉ ይገኛሉ። ይህን ተቀምጠው ማየት ያልቻሉት ወጣት እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ሰራቸውን፣ ትምህርታቸውን፣ ኑሮአቸውን ትተው ዱር ቤቴ ብለው እየታገሉ ይገኛሉ። ይህን እውነት መለወጥ መበረዝ የማይቻል መሬት ላይ ያለ ሀቅ ነው። አማራው ህልውናውን ሳያስከብር ከቶም ቢሆን ላይመለስ ያነሳውን መሳሪያ ላያስቀምጥ ቆርጦ ተነስቷል። ሌላ ምን አማራጭ ነበረው?
በዚህ የህልውና ትግል መሀል መቁሰል፣ መሞት ወይ መማረክ እንዳለ ቢታወቅም፣ ከቶም ቢሆን በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም የማይገባው አረመኔ፣ ሰቅጣጭ፣ ከጭካኔም የጭካኔ ጥግ ያለፈ ወንጀል በአብይ አሀመድ ወታደሮች በሴት እህት አርበኞቻችን ላይ የተፈጸመውን ሰምተንና አይተን ዝም የማንልበት ደረጃ ለይ ደርሰናል። በሌሎች ሚዲያዎች እንደሰማችሁት የተፈጸመውን ዘግናኝ ወንጀል እንደ ቅደም ተከተሉ እናቀርባለን።
1/ መስከረም 30 ቀን 208 ዓ/ም በወገራ የበላይ እዝ 3ኛ ኮር አምባራስ ክፍለ ጦር አባል የሆነችው አርበኛ ፋኒት መቅደስ ተስፋዬን በመግደል ሬሳዋን በመኪና በመጎተት አስፋልት ላይ ጥለው እንዳትቀበርም አስከሬኗን በጸሀይና በዝናብ እንዲበላሽ በማድረግ ዘግናኝ ድርጊት በመፈጸም የአብይ ሰራዊት የተካነበትን የኢሰብዓዊ ባሕሪውን ለሕዝብ አሳይቷል።
2/ ወጣቷ አርበኛ ፋኒት በዓለም ዋሴ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ሰቃይና መከራ፣ ሰደትና መፈናቀል፣ መገደልና መጨፍጨፍ አንገብግቧት ይህን አረመኔ የአብይ አህመድ ፋሽስት አገዛዝን ለመፋለምና ነጻነቷን ለማስከበር ቆርጣ ወስና የህልውና ትግል ከሚያደርገው ፋኖ ጋር በአርበኝነት ተቀላቀለች። አርበኞቹ ለቅኝት ሰራ ወጥተው በአጋጣሚ በተደረገ ውጊያ በዓለም ዋሴ ጥቅምት 2 ቀን 2018 በዓለም በጥይት ቆስላ ተማረከች።
በአረመኔው አብይ አህመድ አገዛዝ ወታደሮች ግን በሀሰት ትርክት፣ በትእዛዝና በጥላቻ የሰለጠኑበት ሰራ ሰለሆነ ይህች ወጣት አርበኛ በዓለም ዋሴ ቆስላ ስትማረክ የፈጸሙባት ተግባር ግን ተሰምቶና ታይቶ የማያውቅ አስቃቂ የጭካኔ ጥግ ነው። ቁስለኛዋን ምርኮኛ ልብሷን አወላልቀው “አማራ” የሚለውን እጇ ላይ የተነቀሰችውን ንቅሳት በጩቤ ገፈው፤ ሁለቱንም ጡቶቿን በሳንጃ ቆራርጠው፣ መላ ሰውነቷን በሳንጃ ስለት ወጋግተው በኢስብዓዊነትና እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ አስከሬኗን መንኩሳ ከተማ መሀል አስፋልት ላይ ጥለው የአረመኔነታቸውን ጥግ ለሕዝብ አሳይተዋል።
3/ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ/ም ደግሞ በራያ በጮቢ በር ግንባር ተጋድሎ እያደረገች የተሰዋችው የምሥራቅ አማራ ኮር አንድ አውጃሮ ክፍለጦር 3ኛ ሻለቃ አባል የሆነችው አርበኛ ፋኒት ትግሥት ወዳጅ ይመር ካስከሬኗ ላይ አንደኛውን ጡቷን ቆርጦ እርቃኗን ሜዳ ላይ ጥሎ ሰቅጣጭና አረመኔያው ድርጊት የፈጸመው በጥላቻ የተሞላው የአብይ አህመድ ሰራዊት ነው።
ይህን ሰምተን ብንደነግጥም ወይም ብናዝንም፣ በሚዲያ ብቻ ሼር አድርገን ስናበቃ እጃችንን አጣጥፈን ከተቀመጥን፤ ነግ ተነገወዲያ መገመትና ማመን ከምንችለው በላይ ተመሳሳይ አስቃቂ ድርጊት በሊሎችም ከተማዎች መስማታችን ወይም በእያንዳንዳችን ቤት ማንኳኳቱ የማይቀር ነገር ነው።
እንደሚታወቀው በተለያዩ ምክንያቶችና ተዳክመንና አንዳንዶቻችን ከትግሉ ለጊዜው ራሳችንን ገሸሽ አድርገን የተቀመጥን ሁሉ፤ እንዲሁም ሆን ተብሎ በብልጽግና ካድሬዎችና በተለያዩ የስርዓቱ ደጋፊዎች ተስፋ የሚያስቆርጡ ዜናዎች ሰምተን ያመንን፣ የትግል አቅጣጫ የሚያስቀይሩ አጀንዳዎችን እየሰጡን አቅጣጫ በመሳት ግራ ተጋብተን የተቀመጥን ሁሉ፤ በዚህ አስከፊና ዘግናኝ ድርጊት ነቅተን ካልጮኽን፣ ለአርበኞቹ እህት ወንድሞቻችን ድምጽ ካልሆናቸው፣ የህልውና ትግሉን ካላገዝንና የድል አቅጣጫ ካላሲያዝን የተደከመው ሁሉ፣ አርበኞቻችን የከፈሉት መስዋዕትነት ሁሉ ከንቱ እንዳይሆን ያሰጋል!
የጀግና እህት አርበኞቻችንን ዓላማና ስም ከፍ አድርገን ይዘን ሕዝባዊ ስብሰባ፣ የሻማ ምሽቶች፣ የተቃውሞ ድምጽ ዘመቻ፣ የህልውና ትግሉን ለድል የሚያበቃ የዲፕሎማሲ፣ የተጠናና ወጤታማ የሆነ የድጋፍ ሰራ መሰራት ይኖርበታል።
አጀንዳ የሚያስቀይሩ፣ የተለያዩ ተቃዋሚ መስለው ወይም ጥሩ ኢትዮጵያዊ መስለው “ሰብዓዊ ሰራ እንሰራለን” እያሉ ባለው አረመኔ አገዛዝ በኩል ገንዘብ የሚልኩትን፤ በወገናቸው ላይ ይህን ዘግናኝ ድርጊትና እልቂት ሲፈጸም እያዩ ቃል ሳይተነፍሱ ቢያንስ እንኳን ሃዘናቸውን ሳይገልጹ፣ አገር እየጠፋ ሕዝብ እያለቀ “የኢንቬስትመንት ሰራ፣ የሰዎች እውቅና፣ የመዝናኛ ዝግጅት እና “ይህን ድርጅት፣ ያንን ማዕከል እንርዳ” በማለት በውጭ የሚገኘውን ሕዝብ ጊዜና ገንዘብ አሟጥጠው የሚያስጨርሱትን ለይተን እንወቅ፣ ለሚያልቀው ለሚጨፈጨፈው ወገናቸውስ ምን ሰራ ሰሩ? ምንስ ተናገሩ? ምንስ አደረጉ? ብለን መጠየቅና አቅጣጫ የማሳት ዓላማቸውን ተረድተን ከነሱ ራሳችንን ማራቅ ይኖርብናል። እንነቃ!
የአማራው ሕዝብ ህልውና፣ የሊሎችም ኢትዮጵያውያን ህይወት፣ የኢትዮጵያ ሰላም ከሁሉ ነገር በላይ እንደሚበልጥ ማሳወቅና በተግባር ማሳየትስ ለምን ተሳነን? ብለን ድክመታችንን አርመን መነሳት የግድ ይላል። ምክንያቱም ትግላችን የህልውና ትግል ነውና!!!
ከሞታቸውም የአሟሟታቸው ሁኔታና ከሞቱ በኋላ በአስከሬናቸው ላይ በአረመኔዎች የደረሰባቸው ድርጊት እጅግ ዘግናኝ በመሆኑ እያወገዝን፤ የሞቱትን ጀግኖች አርበኞቻችንን ነፍስ ፈጣሪ በአጸደ ገነት እንዲያሳርፍልን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለጓዶቻቸው ሁሉ ፈጣሪ መጽናናትን እንዲሰጥ እንመኛለን።
ሰለሆነም በነዚህ ጀግና የሴት አርበኞቻችን ላይ የደረሰውን ኢሰብዓዊና አረመኔያዊ ድርጊት በመላው ዓለም እንዲሰማና እንዲወገዝ በማድረግ፣ ዘረኛውና አረመኔው የአብይ አህመድ አገዛዝ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ በመታገል፤ እኛም ተሰባስበን በአንድነት ቆመን የውጭ ደጋፊ ኃይል ሆነን የህልውና ትግሉን በሙሉ ልብ በመደገፍ፤ በየአገሩ እንቅስቃሴያችን አሳድገን፣ ድምጻችን እንዲሰማ የተለያዩ የተግባር ሰራዎችን እየተወያየንና ጥሩ ግንኙነት በማድረግ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴያችንን ማፋፋም ይኖርብናል እንላለን። በየአገሩ፣ በየአህጉሩ ላሉት የህልውና ትግል ደጋፊ አማራ ሁሉ የአማራ ማኀበረሰብ ድርጅት በቶሮንቶና አካባቢው ጥሪውን በአክብሮት ያቀርባል።
የአማራ ሕዝብ ትግል የህልውና ትግል ነው!
ጥቅምት 9 ቀን 2018
ቶሮንቶ፤ ካናዳ