ህዳር 26፣ 2018 (ዲሰምበር 5፣2025)
ኢህአፓ ህጋዊና መሰረታዊ መብቱን በመጠቀምና ህጋዊ መንገድን በመከተል አዲስ አበባ ላይ ለህዳር 27፣ 2018 (December6, 2025) የህዝብ ስብሰባ ለማድረግ ዝግጅቱን ሁሉ አጠናቆ እንደነበር በሰፊው ይታወቃል። የአዲስ አበባ ወታትም ይህን ሰብሰባ ለማታደም በከፍተና ጉኡት ሲጠብቅ እንደነበር የተለያዩ መረጃዎች አሳይተዋል፡፡
ሆኖም ግን በመጨረሻው ሰዓት ላይ ብልፅግና ስብሰባው እንዳይካሄድ በቀጥታም ይሁን በተዘውዋዋሪ መንገድ የተለመደዉን የዲሞክራሲ ሆነ የዜጎች በነፃነት የመስብሰብ መብት አፈናዉን በመጠቀም ስብሰባው እንዳይካሄድ አድርጓል፡፡
በዚህ ተግባሩ ብልጽግና ፀረ ዴሞክራሲነቱን ይበልጥ አያረጋገጠ ብቻ ሳይሆን ህዝቡን ከአዳራሽ ውስጥ ስብሰባ በላይ ለከፋ አመፅ እንዲዘጋጅ እያደረገውም ጭምር ነው።
ብልጽግና ለህዳር 27፣ 2018 ኢ ህ አ ፓ የጠራውን ህዝባዊ ስብሰባ በሰላም እንዲካሄድ ሊፈቅድ እንደማይችል ቀደም ሲልም ተገማች ቢሆንም በተለይም ምርጫ ይካሄዳል በሚባልበት በአሁኑ ሰዓት መሆኑ ደግሞ በሀገራችን ወስጥ ነጻና የህዝብ ፍላጎት በትክክል የሚገለጥበት ምርጫ ለማካሄድ እንደማይቻል የህዝብን መሰረታዊ መብት ማክበር የአገዛዙ ፍላጎት እንዳልሆነ ይበልጥ የተረጋገጠበት ይፋ ማስረጃም ነው፡፡
ህዝብ የሚፈልገውን ለመምረጥ አማራጮቹ እነማን እንደሆኑ ማውቅ መብቱ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ መሰብሰብንና በተቃዋሚነት የቆሙ አማራጭ አይሎች የሚያቀርቡትን ራዕይ ማወቅ የሚችልበት ምህዳር እንዲኖር ግድ ይላል፡፡ ባለፉት ስባት የአገዛዝ ዘመኑ ብልጽግና ምን እንደሆነ በግልፅ የሚታወቅ ቢሆንም በዚህ የስብሰባ ማደናቀፍ ተግባሩ ደግሞ እውነተኛ ገጽታውን ፀረ ዴሞክራሲና አፋኝ አገዛዝ መሆኑን ይበልጥ እንዲታይ አድርጓል፡፡ ይህ ህዝባችን ሊሸከመው የማይችለውና የማይገባውም ዘኛኝ ጉዳይ ነው፡፡
ኢሕአፓ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ጠርቶት የነበረው ስብሰባ ህዝቡ በዕለት ተዕለት ህይወቱ እየገጠመው በሚገኘው ማቆሚያ የሌለው የከፋ የኑሮ ውድነት፤ ራሱንም ቤተሰቡንም ለማቆየት የዕለት ጉርስ፣ለመጠለያው የቤት ኪራይ የሚሆን አጥቶ ባለበትና አጠቃላይ ኑሮውን አሣዛኝና እጅግ አስጨናቂ ባደረገው የሀገሪቱ ሁኔታ ላይ ለምመካከር ነበር፡፡ ጥሪው የህዝብ ብሶት መገለጫ የህዝብንም ብሶት ማሰተጋቢያ ነበር ፡፡
ስብሰባው ህዝብ በሰበብ አስባቡ፣ ወደ እስር የሚወረወርበት፤ በልማት ስም ዜጎች በግፍ የሚፈናቀሉበት፣ በማንናታቸውና በእምነታቸው የሚሳደዱበት የሚዋከቡበት የሚገደሉበት ሁኔታ ለመነጋገር ዜጎች በሰላምወጥተው መግባት አስተማማኝ ባልሆነበት፣ በዚህ አገዛዝ ስር ንብረታችው እየተነጠቀ በልማት ስም እንደእቃ የሚወረወሩበት ጉዳይ ላይ ለመወያየት ይህም የሚያበቃበትን በጋራ ለመመልከት ነበር፡፡
ስብሰባው ወጣቱ ሥራ ማግኘት ለምን አንዳልቻለ፣ በሀገሩ እንደልቡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መሥራትም ሆነ በሰላም መኖር ለምን አንዳልቻለ፣ አንገቱን ቀና አድርጎ መሄድ ለምን እንዳልቻለ፣በሀገራችን ውስጥ የሚታየው ወገኖቻችንን እየጨረሰ የሚገኘው ጦርነት ምክንያቱ ምን እንደሆነ፣ በአጠቃላይም ወጣቱን አዛውንቱንም ሴቱንም ወንዱንም እያስጨነቀና ተስፋ እንዲያጣ እያደረገው ያለው ምን እንደሆን በጋራ እንዲመካክርና በጋራም መፍትሄ እንዲፈልግ ለማድረግ ነበር፡፡
ከዚህ በተፃራሪ ብልፅግና የወሰደው ዕርምጃ፣ ይህን የህዝብ ብሶት ህዝብ እንዳይነጋገርበት ማድረግ፣ ህዝብን በዚህ ሰቆቃ ስር በፍርሀት ተሸብቦ በስልጣን ለመቀጠል እንጂ ችግሩን ለመፍታት በፍጹም እንደማይፈቅድ ማሳያ ነው፡፡ ህዝብ ደግሞ በባርነት ሰቆቃ መኖር አይገባውም አይፈልግምም፡፡
ህዝብ ይህን የራሱን ጉድይ ለመነጋገር የሚችልበት የስብሰባ አዳራሽ ግብር እየከፈለ በሚኖርብት የራሱ በሆነችውና እጅግ ብዙ አዳራሽ በሚገኝባት ከተማው በአዲስ አበባ እንድ አዳራሽ ለተወሰኑ ሰዓቶች መከልከሉ ህዝብ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚፈቀድለት የበይ ተመልካች ሆኖ እንዲኖር ብቻ መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ ይህ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም በትግስት ሊታለፍም አይገባም፡፡
ከላይ የተገለጠው የአገዛዙ ተግባር ሁሉ ሀገወጥ ብቻ ሳይሆን ከህዝብ ፍላጎት በተጻራሪ የቆመ ህዝብን ለበለጠ ተስፋ መቁረጥ ፣ ለበለጠ ድህነት፣ ለበለጠ መፈናቀል ለበለጠ ብስጭት ወዘተ የሚዳርግ ሀገርንም አደጋ ላይ የሚጥል ነውና በጥብቅ ልንቃወመውና ልንታገለው ይገባል፡፡ ገዝዎቻችን ኢትዮጰያንም ይሁን ህዝባችንን እንደፈለጉ እንዲያደርጓቸው መፍቀድ እጅግ አስነዋሪ ብቻ ሳይሆን በታሪክም አስወቃሽ ነውና ምንም አይነት ቅቡልነት ሊኖረው አይገባም አይችልምም፡፡
የህዝባችን ትግል አሁንም ሀገርን ለማጽናት ህዝቡም ሙሉ መብቱን እንዲጎናፀፍ እንጂ በግፈኞች ስር ተንበርክኮ የፈለጉትን ቀንበር ጭነውበት እንዲኖር አይደልም ፡፡፣ ኢሕአፓ ይህ እንዲሆን በፍጹም አይፈቅድም፡፡ እንደድርጅት የሕዝባችንን ዕኩልነት ነጻነት፣ የመብት መከብር ወዘተ እስኪረጋገጥ የሀገራችንም አንድነት በማይናወጥ መሰረት ላይ
እስኪቆም ድረስ አስፈላጊውን መስዋእትነት እየከፈለ ትግሉን ይቀጥላላ እንጂ ሸብረክ አይልም፡፡ ለዚህም መሥረታዊ ዓላማ እንታገላለን የምትሉ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ከኢሕአፓ ጎን በመቆም በምትችሉት ሁሉ መንገድ እንድታግዙት እንጠይቃለን፡፡
ይህ የአዳራሽ ክልከላና ማደናቀፍ ትግሉን ይበልጥ እንድናጠናክር እንጂ ወደ ኋላ እንድናፈገፍግ አያደርገንም፡፡
እኛ በውጭ ሀገር የምንገኝ የ ኢህ አፓ ደጋፊዎችም ድርጅቱ ለህዝባችን ለወገንኖቻችን ለሀገራችን ከሚያካሂደውን ትግል ጎን የቆምን መሆኑን አሁንም እናረጋግጣለን፡፡ በሁሉም ቦታ የሚገኙ ለዴሞክራሲ ለአንድነት ለእኩልነት የቆሙ ሁሉ በኢህአፓና በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ የተደረገውን በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ በሰላም የመሰብሰብ መብት ክልከላና የማደናቀፍ ተግባር እንዲያወግዙና የትግል አንድነታቸውንም በሁሉም መልክ እንዲገልጹ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
የህዝባችንን መሰረታዊ መብት ለማስከበር በጽናት እንታገል፡፡
ደል ለኢትዮጵያ ህዝብ
የ ኢሕአፓ የውጭ ድጋፍ አስተብባሪ ኮሚቴ