November 30, 2025
ስለ ኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ
ጠቅላላ ዓመታዊ ጉባኤ
የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ!
የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ አጠቃላይ ዓመታዊ የዙም ጉባኤውን ከ70 በላይ የሚሆኑ እንግዶች በማስተናገድ ቅዳሜ ኅዳር ፲፫ ቀን ፪፼፲፰፤ (November 22, 2025) ተካሂዶ፣ በጣም በተሳካ መንገድ ተከናውኗል።
ጠቅላላ ጉባኤው ከመጀመሩ በፊት በትብብሩ ሊቀ መንበር ጋባዥነት፣ በምስራቅ አርሲ በኦርቶዶክስውያን ላይ የሚካሄደውን ግድያ በማስታወስ፣ በአማራ ክልል በድሮን እየተጨፈጨፈ ያለውን ሰላማዊ ሕዝብና የሴቶች መደፈርን፣ እንዲሁም በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች በግፍ የሚያልቁትን በመዘከር፣ የአንድ ደቂቃ የኅሊና ፀሎት ተደርጏል።
የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች፣ ትብብራችንን የመሠረቱ ድርጅቶችና አባላት፣ ዓላማችንና ትግላችንን ያግዛሉ ብለን የጋበዝናቸው ታላላቅ አገር ወዳድ ግለሰቦች፤ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከካናዳ፣ ከጀርመን፣ ከብሪታንያ፣ ከኖርዌ፣ ከስዊድንና ከስዊዘርላንድ ነበሩ።
ለትብብሩ ጠቅላላ ጉባኤው የሚከተሉት ርዕሶች ቀርበዋል፦
1ኛ፣ የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ ከተመሠረተበት አንድ ዓመት ጊዜ አንስቶ የፈፀማቸውን ተግባራትና ግዳጆች፣ እንዲሁም፣ ለማሸነፍ የመተባበርን እጅግ አስፈላጊነት በተግባር ያሳየና ያበሰረ ሪፖርት፣ በሊቀ መንበሩ፣ በዶር ባደገ ቢሻው ቀርቧል።
2ኛ፣ የትብብሩ የፋይናንስና ኦዲት አጠቃላይ ሪፖርት፣ በፋይናንስ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ በአቶ ከፍያለው ፈቃደ፣
፫ኛ፣ የትብብሩ መተዳደሪያ ደንብና የሥነ ምግባር መመሪያ ሰነዶች፣ እንዲሁም፣ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ለመተባበር የወጣ የአቋም መግለጫና መመሪያ ሰነድ፣ በዶ/ር ኦፒኦ ቻም፣
፬ኛ፣ የትብብር ንቅናቄው ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ፣ ሰላምና ፍትህ ለማስገኝት ለሚቀጥሉት ዓመታት ስለሚያደረገው የታቀደ ትግልና ሊያስከትል ስለሚችለው ረቂቅ ፍኖተ ካርታ፣ በኢንጅነር ሰለሞን ገ/ስላሴ፣
፭ኛ፣ ስለ ሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የተነደፈ የትግል ስትራተጂና በዚያም ላይ ተመሥርቶ ለበርካታ ሳምንታት ስለተደረጉ ጥናቶች፣ ምርምሮችና ውይይቶች እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ስለተቀሰሙ ልምዶች፣ ከዚያም አልፎ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እንዴት በተግባር ሊተረጎም ስለሚችልበት ብልሃትና ዘዴ፣ አያይዞም በተለያዩ ሚዲያ አውታሮች ስለሚሰራጨው ሕዝብን የማስተማርና የማንቃት ዘመቻ ዝርዝር ዘገባ፣ በአቶ ነአምን ዘለቀ ቀርቧል።
የጠቅላላ ጉባኤውን ሂደት ሁለት ሊቀ መንበሮች በፈረቃ ሲመሩት፣ በፖወር ፖይንት የተደገፋት አቅራቦቶች ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ሲያስነሱ፣ ጥልቅ ዲሞክራሲያዊ ውይይቶች የተካሂዱባቸው፣ የተለያዩ ሃሳቦች መንሸራሸር የታዩባቸው፣ ገንቢ ምክረ ሃሳቦች የቀረቡባቸው ነበሩ።
ይህ ጠቅላላ ጉባኤ የሚከተሉትን አበይት ቁም ነገሮች ለኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ አስጨብጧል። አንደኛ፣ “ስንተባበር እናሸንፋለን” የሚለውን መፈክርና መርኅ አጠናክሮ የትብብሩን ድርጅታዊ መዋቅር፦ በአውሮፖ፣ በኤሲያና በአፍሪካም አስፍቶ፣ ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቋቋም ግዙፍ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ጉልበት እንዲገነባ ከሙሉ መግባባት ተደርሷል።
ሁለተኛ፣ አሁንም ውድ አገራችን ኢትዮጵያ የገባችበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ውዝግቦች በማጤን፣ የአብይ አህመድ የብልፅግና መንግሥት ይህችን አገር ለከፋ አደጋ ሊዳርጋትና መንግሥትም ራሱ ከስልጣን ሊወርድ እንደሚችል በማጤን፣ የአገራችንን አንድነት ያስጠበቀ፣ ዲሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደትና የመንግሥት ምስረታ ጉዳይ አሁኑኑ ቅድሚያና አፅንኦት ተሰጥቶት፣ ትብብሩ ከሌሎችም በኢትዮጵያ አንድነት ክሚያምኑ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በመተባበር ብልሃትና ትልም እንዲነድፍ ከጉባኤው ተሳታፊዎች ምክረ ሐሳብ አስገንዝቧል።
ትብብሩ ይህን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማዳን የሚታገሉ ኃይሎችን ሕብረትና የሽግግር ሂደት ጉዳይ በሚመለከት በጥናት ላይ የተመረኮዘ፣
የተለያዩ ሐሳቦች የሚስተናገዱበት ውይይት የሚካሄድበት ጉባኤ ጥር (January) አጋማሽ በመጥራት፣ በንደፈ ሐሳብ ደረጃ አንድ አግባቢ ዕቅድ ለማስቀመጥ እንደሚጥር ተገልፆአል።
በተረፈ የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ አባል ድርጅቶችን፣ እንዲሁም የድርጅቶች አባላትን ሊያኮራና ሊያበረታ የሚችል፣ በዝግጅትም፣ በሪፖርቶችና በጥናት አቀራረብም፣ በዲሞክራሲያዊ ውይይት አካሄድም፣ በተሳትፎም እጅግ የተሳካለት ጉባኤ መከናወኑን በመገንዘብ፣ ይህ ውጤት ለወደፊት ትግላችን ትልቅ ስንቅና ጉልበት እንደሚሆን አባላት በሙሉ በመግባባት አምነውበታል።
በትብብራችን እናሸንፋለን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
የኢትዮጵያዉያን ትብብር ንቅናቄ፣