ይድረስ ለውድ ወገኖቼ
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች
ወግኖቼ እንዲያው ቢጨንቀኝ እንጂ ችግሩ የእኔ ብቻ ሁኖ አይደለም ከፊታችሁ መቆሜ
ተወልጄ ያደግሁት በዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ስሆን በረጅም ጊዜ ልፋት ከስድሳ ዓመት በፊት የገዛሁት በጣም ሰፊ ይዞታ ነበረኝ በውስጡም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች ለምተውበታል። ሁለት ለስራ የደረሱ ልጆቼ ከቤታችን ግቢ ውስጥ በስተግራ አንዱ ልጄ ጥሩ ሸማኔ በመሆኑ የሽመና ስራ ይሰራበታል፤ ሌላኛውም ልጄ የተዋጣለት የእንጨት ስራ ባለሙያ በመሆኑ ከልጆቹ ጋር የተለያዩ የቤት እቃዎችን ይሰራበታል። እንዲያው ለአትክልቱም ለፍራፍሬዉም ተንክባካቢ አስፈለገኝና በዚያ ሰሞን የንብረቴ አስተዳዳሪ የሚሆን ማለፍያ ሰው ለመቅጠር እንደምፈልግ ለወዳጅ ዘመዶቼ መንገሬን የሰማ አንድ መልከ መልካም አንደበተ ርቱእ የሆነ ጎልማሳ “አብዬ ስጦታው” እያለ እየተቅለሰለስ ከቤቴ በመምጣት ባለቤቴንም እምዬ ምንትዋብ እናቴ የናንተ የእናቶች ምርቃትና ጸሎት እዚህ አድርሶኛልና አሁንም ይህንን ንብረታችሁን እንደእናንተ ሁኜ ላስተዳድር ፍቀዱልኝ ከማለት ባሻገር አብዬ ይህንን ቦታ ቀደም ብዬ አውቀዋለሁ የመስኩ መሃንዲሶችም ሲናገሩ ሰምቻለሁ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት ያለበት ግቢ ነውና በአጭር ጊዜ ነዳጁ እንዲወጣ አስደርግሎታለሁ እርስዎም ሆኑ ቤተስብዎ የበለጸገ ኑሮ ይኖራል በማለት ንብረቴን እንዲያስተዳድር ለአምስት አመት ውል ገብቼ ቀጠርኩት።
ይህም አስተዳዳሪ ያልኩት ጎልማሳ ብዙም ውሎ ሳያድር አብዬ ከዚህ ከቤትዎ ውጭ ያለውን ይዞታ ሰዎች ቢሰፍሩበት ጥሩነው ለእርሶም ሰው ይሻሎታል ብሎኝ ብዙ ሰዎች ሰፈሩበት። ጥቂት ቆይቶም ሰዎቹ ከተማ መመስረታቸውን ስሙንም ሽብርታ ማለታቸውን ሰማሁ። ይግረማችሁና በከተማ ላይ ከተማ ሲመሰረት ይህ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም። እኔም ወገኛ ነኝና አስተዳዳሪዬን ባለፈው ሰዎቹ ሲሰፍሩ ምን ብለሔኝ ነበር ሲለው አቢዬ መሬቱ እኮ የአያቶቻቸው ነው ብሎኝ እርፍ። እኔም አቅሜ እየደከመ መሄዱ ላይ ሁለቱም ዩኒቨርሲቲ የጨረሱት ልጆቼ ስራ ፍለጋ ላለፉት ሶስት አመታት ከቢሮ ቢሮ ይንከራተታሉ። በስተርጅና የወለድኩት ልጄም አስራ ሁለተኛ ከፍል ማለፍ አልቻለም። እሱንም ለመጦር ተገድጃለሁ። አስተዳዳሪዬ አብዬ የሚመጣው ብልጽግና ለሁሉም ይበጃል ብሎኝ የኮሪደር ልማት ልናለማ ነው ብሎን የሽመና ቤቱንም የእንጨት ስራ ቤቱንም አፍርሶብን ልጆቼ ለስራ በቂ ትክ ቦታ አልተሰጣቸው ያለ ካሳ ከከተማ ውጭ ተጥለው ችግር ላይ ናቸው። ለኮንዶሚንዬም ቤት ብለው ቢመዘገቡና ገንዘብ ቢቆጥቡም ሊደርሳቸው አልቻለም። ትልቁ ልጄ ጳውሎስ በጋራዥ ስራ ይተዳደር ነበር አሁን ኑሮ በመወደዱና ከመሃል የነበረው ህዝብ ወደዳር በመውጣቱ ገበያው ከመቀዝቀዙ ባሻገር የተጣለበትን ግብር መክፈል ባለማቻሉ ጋራዡን ዘግቶታል። ኢትዮጵያ ስጦታው “ሴቷ ልጄ” አባዬ እመጣለሁ የሚል ማስታወሻ ብቻ አስቀምጣ ከቤት ከወጣች ድፍን ሁለት አመት ሆናት፤ አንዳንዱ ሰው በጂቡቲ በኩል ሳትወጣ አትቀርም ሲል ሌላው ተቀብሎ በሱዳን በኩል ሊቢያ ገብታለች ይለኛል። የአብዬ ስጦታው ቤተሰብ እንዲህ ሆነላችሁ ወገኖቼ።
በገዛ እጄ የቀጠርኩት አስተዳዳሪዬ ያመጣብኝ መከራ በዚህ አላበቃም ጎጃም የሚገኙት ዘመዶቼ አልፎ አልፎ ሊጠይቁኝ ሲመጡ ጤፍ ማር ቅቤም ያመጡልኝና የኑሮ ውድነቱን በመጠኑ እደጉመው ነበር፤ በነበር ሆኖ ቀረና ዘመዶቼም እኔ አለሁበት አዲስ አበባ ከተማ አትገቡም ተብለው በስቃይ ላይ ነን።
አስተዳዳሪዬ ዘወትር ህዝባችንን የምናስተዳድረው በሕገ መንግስቱ ነው እያሉ ሲናገሩ ስምቼ አንዱን ዩኒቨርስቲ የጨረሰው ልጄን እባክህን ይህ ሕገ መንግስት የሚባለው ነገር እኔን ያውቀውኝ እንደሆን አንብብልኝ ብለው አይ አባዬ ህገመንግስቱ የሚለው ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች እንጂ አንተ ሁሌ እንደምትለው ዜጎችን አያውቅምና አርፈህ ተጦር አለኝ። መከራው ይብቃኝ ብዬ ፈጣሪዬን ብለምነውም ከቀን ወደ ቀን እየከበደኝ መጣ። የአስተዳዳሪው አስከፊ ጭካኔ እኔ በወር የማገኘው የጡረታ አበል አንድ ሺህ ብር ሲሆን የጣራና ግድግዳ ቀደም ሲል የምከፍለው መቶ አምሳ ብር ነበር አሁን ግን ሃያ ሺህ ብር አለኝ ምድር ሰማዩ ተደፋብኝ።ወዴት ልድረስ !!
ሙሉ ስሜ ስጦታው ሃጎስ ቶሎሳ እባላለሁ ይሄው ላለፉት አርባ አመታት በስሜ ብቻ የመንፈስ ጭቆና ደርሶብኛል፡፤ የመጀመሪያ ስሜን ያዬ ነፍጠኛው፤ ያለፈው ስርአት ናፋቂ ሲለኝ፤ ሁለተኛውን ወይም የአባቴን ስም ያዬ የቀን ጅብ ብሎ ያላግጥብኛል በአያቴ ስም ደግሞ ባለ ጊዜው ተረኛው እየተባልኩ ተሰቃየሁ ወይ የአዲስ አበባ ልጅ!!
ወገኖቼ እንዲህ ሲቃዬን ያበላኝ የኔው አስተዳዳሪ ብቻ ነው ወይስ የናንተም ይሆን?። እኔ የመጣው ይምጣ ከዚህ የባሰስ አይመጣብኝና የቅጥር ጊዜውን ስለጨረሰ ሌላ አስተዳዳሪ ለመቅጠር ወስኛለሁ እናንተስ??
አመሰግናለሁ!!
አዲስ አበባ
ሕዳር 27 ቀን 2018 ዓ.ም