የተፈራው ደረሰ!! ያሳዝናል!!
*ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ*
ኢሕአፓ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱት በራሱ በኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ ሰላማዊ ትግል ነው ብሎ በጽኑ ያምናል። ፓርቲያችን ከቆመለትና ለመብቱና ጥቅሞቹ መጠበቅም ከሚታገልለት ህዝብ ጋር ለመወያየት ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2018 ዓ.ም በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ከረጅም አመታት በኋላ የመጀመሪያ የሆነውን ህዝባዊ ስብሰባ “አዲስ አበባ ትናገራለች” በሚል መሪ ቃል ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው ሆቴል ዲ’አፍሪክ የሚያካሂድ መሆኑን ማስታወቁ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ባሰለፉት ሳምንታት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች ጥሪ ሲያስተላልፍ ቆይቷል።
የአዲስ አበባ ነዋሪም በህዝባዊ ውይይቱ ላይ ተገኝቶ ሀሳቡን ለመግለጽና ለበርካታ ሀገራዊ ችግሮችም በጋራ የመፍትሔ አቅጣጫ ፍለጋ ላይ ለመምከር አቅዶ የነበረ መሆኑን እና ለሕዝባዊ ስብሰባውም ድጋፉን በተለያየ መንገድ ሲገልጽልን ሰንብቷል።
ለሕዝብ መገልገያነት መዋል የሚገባቸው የመንግስት አዳራሾች በስርኣቱ ሙሉ ቁጥጥር ውስጥ በመሆናቸው እና በአዳራሾቹ የመገልገል መብታችንን እንደ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ መብቶች ሁሉ ስለተነጠቅን የግል አዳራሾችን ለማነጋገር ተገድደናል፡፡
ነገር ግን ያነጋገርናቸው ሆቴሎች፣ ሲኒማና ትያትር ቤቶች እንዲሁም የግል አዳራሾች በሙሉ በቅድሚያ ፈቃደኝነታቸውን ገልጸውልን ውል ለመዋዋል ጫፍ ላይ ስንደርስ በማናውቀው መንገድና ምክንያት ሊያከራዩን እንደማይችሉ ሲገልጹልን ቆይተዋል፡፡
በመጨረሻም ኢሕአፓ ከሆቴል ዲ’አፍሪክ ጋር የአዳራሽ ኪራይ ውል ተፈራርሞ የመጀመሪያ ክፍያ ፈጽሞና ሌሎችንም ለህዝባዊ ውይይቱ አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን መሰናዶዎች አድርጎ ሕዳር 27ን ሲጠባበቅ ሰንብቷል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ስርኣቱ በአንድም በሌላም መንገድ ሕዝባዊ ስብሰባውን እንዳናካሂድ ሊያደርግ እንደሚችል እኛ ብቻ ሳንሆን ኢሕአፓ በሚያደርገው ሰላማዊ ትግል ተስፋ አድርጎ ከጎናችን የቆመው ሕዝብም በተደጋጋሚ ሲያሳስበን ቆይቷል፡፡ በእርግጥም ሀገራችን የምትገኝበት ሁኔታ ከሕዝብ ጋር በነፃነት ሃሳብን ለመለዋወጥ እንደማያስችል በተግባር ተረጋግጧል፡፡
ይህ ስብሰባ እንደሚደረግ ካሳወቅንበት ቀን ጀምሮ የስርኣቱ ልሳን መሆናቸውን በተደጋጋሚ በተግባራቸው ያረጋገጡ አክቲቪስቶች እና የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች በፓርቲያችን እና በአመራሩ ላይ የሰነዘሯቸው መሰረት የለሽ ውንጀላና ስም ማጥፋቶች የሕዝብ መከራን ጉዳዬ ባላሉ ተለጣፊዎችና በብልጽግና ዘንድ ሕዝባዊ ስብሰባ መጥራት የሚያስከስስ እና የሚያስወጅል መሆኑን በግልጽ አሳይቷል፡፡
ፓርቲያችን የስም ማጥፋቱንም ሆነ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የሚደርሱበትን በቃላት ሊገለጹ የማይችሉ ጫናዎች ተቋቁሞ ስብሰባውን የገፋበት ቢሆንም በ11ኛው ሰኣት ሆቴል ዲ’አፍሪክ ምንም አይነት አጥጋቢ ምክንያት ሳይሰጥ “ውሉን ሰርዣለሁ፤ የከፈላችሁትን ገንዘብ ውሰዱ” ሲል ውል ማቋረጡን አሳወቀን።
መቼም የተቋቋመው በኪራይ እና መሰል አገልግሎቶች ገቢ ለማግኘት የሆነ የንግድ ተቋም ከቁጥጥሩ በላይ የሆነ ሁኔታ ባያጋጥመው በመጨረሻው ሰኣት ይህንን እንደማያደርግ እናውቃለን።
ውሉን ያለአሳማኝ ምክንያት በማፍረሱ ሆቴሉን ልንከሰው ብንችልም በግድ ሆቴሉ ውስጥ ለመሰብሰብ ግን ስለማንችል በአደራሽ መከልከል ምክንያት ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2018 ዓ.ም ሊደረግ የታሰበውና ዝግጅቱም ተጠናቅቆ በጉጉት ይጠበቅ የነበረውን ህዝባዊ ስብሰባ ላለማድረግ መገደዳችንን ለተከበረው የአዲስ አበባ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ እናስታውቃለን። በኢትዮጵያ ውስጥ ከሕዝብ ጋር መወያየት በፍጹም የማይቻል ሆኗል፡፡
ይህን ዐይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ነው፣ “ድንቄም ዴሞክራሲ” እንድንል የምንገደደው!! በዚህ ሁኔታ በተደጋጋሚ ከስርኣቱ አፎች እየሰማን እንዳለነው በነጻነት፣ርዕቷዊነት፣ ተአማኒነት የሚኖረው ጠቅላላ ምርጫ ውስጥ ፓርቲዎች ለመሳተፍ የሚችሉት እንዴት ነው??!!
ለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ ሕዝብን ሰብስቦ ለማወያየት ካልቻለና የሃሳብ ልውውጥ ለማድረግ የማይችል ከሆነ የገዢው ፓርቲ አጫፋሪ ከመሆን ውጪ ምን ሊፈይድ ይችላል??!! ይህ ሁነት ይህንን እና መሰል በርካታ ጥያቄዎችን እንድናነሳ የሚያስገድድ ነው፡፡
ስርኣቱ በጽሑፍ ‹ስብሰባውን ፈቅደናል› ቢልም በማይታየው እጁ ከጀርባ መከልከሉን በተደጋጋሚ ከተስማሙ በኋላ ሃሳባቸውን መቀየራቸውን በሚነግሩን ለዚህ ስብሰባ ያነጋገርናቸው አዳራሾችና ሆቴሎች ሁነት እንዲሁም ስርኣቱ በፓርቲው ላይ ከከፈተው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ለመረዳት የፖለቲካ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም፡፡
ነገር ግን አዳራሽ በመከልከል እና በማስከልከል የሚቆም የኢሕአፓ ትግል የለምና በቀጣይ አዳራሽ በማይጠይቁ የሰላማዊ ትግል አማራጮች ወደ ሕዝብ እንደምንደርስ በእርግጠኝነት ለመናገር እንወዳለን፡፡ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሌም ኢሕአፓ በሚያደርገው ጠንካራ እና የማይበገር ሰላማዊ ትግል ከጎኑ እንዲቆምም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የዜጎችን የመሰብሰብ እና የመቃወም መብቶች ላይ የሚደረግ ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ የአገዛዙ ክልከላ ሰላማዊ ትግሉን ማስቆም በፍጹም አይችልም!!
ዘላቂ ድል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ!!
ሕዝብ ሁሌም አሸናፊ ነው!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ
ህዳር 26 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
ስልክ/Phone +251 115570366 ኢሜይል/Email፡ eprp@eprp-hapa.com